1 Samuel 10

1ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ፣ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ እንዲህ ሲል ሳመው፤ “በርስቱ ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶህ የለምን
የዕራይስጥ ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ የሰብዓ ሊቃናትና የቩልጌት ትርጕም ግን፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ትገዛለህ ከከበቡት ጠላቶቹም እጅ ታድነዋለህ፤ እግዚአብሔር ለርስቱ ገዥ አድርጐ የሾመህ ምልክቱ ይህ ነው የሚለውን ይጨምራሉ።
?
2ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፣ በብንያም ወሰን ላይ በምትገኘው ጼልጻህ በተባለች ስፍራ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፣ ‘የምትፈልጋቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፣ “ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” እያለ በመጨነቅ ላይ ነው’ ይሉሃል።

3“አንተም ጕዞህን በመቀጠል በታቦር እስካለው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ትሄዳለህ፤ እዚያም ሦስት ሰዎች፣ አንዱ ሦስት የፍየል ግልገል፣ ሌላው ሦስት ዳቦ፣ ሌላው ደግሞ የወይን ጠጅ የተሞላበት አቍማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል። 4እነርሱም ሰላም ይሉሃል፤ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ትቀበላቸዋለህ።

5“ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስህም የነቢያት ጉባኤ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በእንቢልታና በበገና ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ። 6የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። 7እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና።

8“ከፊቴ ቀድመህ ወደ ጌልገላ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን
በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል።
ለማቅረብ ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ነገር ግን ወደ አንተ መጥቼ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስክነግርህ ድረስ ሰባት ቀን መቈየት አለብህ።”

ሳኦል ነገሠ

9ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ። 10ጊብዓ በደረሱ ጊዜ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ። 11ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፣ እርስ በርሳቸው፣ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ።

12በዚያ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው፣ “የእነርሱስ አባት ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ፣ “ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ። 13ሳኦል ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ሄደ።

14በዚህ ጊዜ የሳኦል አጎት እርሱንና አገልጋዩን፣ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

እርሱም፣ “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤ እንደማይገኙ በተረዳን ጊዜ ግን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው።

15የሳኦል አጎትም፣ “እባክህ፣ ሳሙኤል ያለህን ንገረኝ” አለው።

16ሳኦልም መልሶ፣ “አህዮቹ መገኘታቸውን ገልጦ ነገረን” አለው። ይሁን እንጂ ስለ መንገሡ ሳሙኤል የነገረውን ለአጎቱ አልተናገረም።

17ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ምጽጳ ወደ እግዚአብሔር ፊት ጠርቶ፣ 18እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤልን ከግብፅ አወጣሁት፤ ከግብፃውያን እጅ ይጨቍኗችሁ ከነበሩት ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ እጅ ታደግኋችሁ።’ 19ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ የሚያድናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ፤ ‘የለም፤ ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። ስለዚህ በየነገዳችሁና በየጐሣችሁ ሆናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቅረቡ።”

20ሳሙኤል የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ ባቀረበ ጊዜ፣ የብንያም ነገድ ተመረጠ። 21ከዚያም የብንያምን ነገድ በየጐሣው ወደ ፊት አቀረበ፤ የማጥሪ ጐሣም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ። እርሱ ግን ተፈልጎ አልተገኘም። 22ሰዎቹም፣ “ሰውየው መጥቷልን?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ።

እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ነገር ግን በዕቃ መካከል ተሸሽጓል” አለ።

23እነርሱም ሮጠው ከተደበቀበት አመጡት፤ በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜም ቁመቱ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ ነበር። 24ሳሙኤልም መላውን ሕዝብ፣ “እግዚአብሔር የመረጠውን ሰው አያችሁን? ከሕዝቡ ሁሉ የሚስተካከለው ማንም የለም” አለ።

ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” ብሎ ጮኸ።

25ሳሙኤልም ለንጉሥ የሚገባውን ወግና ሥርዐት ለሕዝቡ ገልጦ ካስረዳ በኋላ በመጽሐፍ ጽፎ በእግዚአብሔር ፊት አኖረው። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱን ሰው ወደየቤቱ አሰናበተ።

26ሳኦልም ጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ፤ እግዚአብሔርም ልባቸውን የነካው ኀያላን ሰዎች አብረውት ሄዱ። 27አንዳንድ ምናምንቴ ሰዎች ግን፣ “እንዲህ ያለ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” በማለት ናቁት፤ ስጦታም አላመጡለትም። ሳኦል ግን ዝም አለ።

Copyright information for AmhNASV